የልደታ ክ/ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት የሚከተሉት ስልጣንና ኃላፊነት ይኖሩታል
- የክፍለ ከተማ አስተዳደሩን የስፖርት ትምህርትና ሥልጠና ማዕከላትን፣ የስፖርት ማዘወተሪያዎች፣ የስፖርት ልህቀት ማዕከላት እና የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን ያስተዳድራል፤ እንዲስፋፉና አቅማቸው እንዲገነባ ያደርጋል፤
- በክፍለ ከተማ አስተዳደሩ ህጎች ሲተገበሩ የወጣቶችን ሁለንተናዊ መብትና ጥቅም የሚጠብቁ መሆናቸውን ይከታተላል፤ ሁሉም አስፈፃሚ አካላት የወጣቶችን ጉዳይ በዕቅዳቸው ማካተታቸውን ይከታተላል፤ መፈጸሙን ያረጋግጣል፤
- ለወጣቶች መብት፣ ጥቅም እና ደህንነት የሚሰሩ ማህበራት እንዲደራጁና እንዲጠናከሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፤ የወጣት መብት መጣሱን መረጃ ሲደርሰው ጉዳዩን ከሚመለከተው አካል ጋር በማጥናትና በማጥራት የህግ ከለላ ማግኘት እንዲችሉና ተገቢው መፍትሔ እንዲሰጥ ያደርጋል፤
- የወጣቶችን አቅም የሚያጎለብቱ ትምህርታዊ፣ ሙያዊና የተጨማሪ ክህሎት ስልጠናዎችን ያዘጋጃል፤ ያመቻቻል፤ ይሰጣል፤ ከሚመለከተው አካል ጋር በመቀናጀት በተለያዩ በኪነ-ጥበብ በቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ያበረታታል፤ ድጋፍ ያደርጋል፤
- አግባብ ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ወጣቶች በማህበር እንዲደራጁ፣ የመስሪያ ቦታ እንዲመቻችላቸው፣ የማምረቻ መሳሪያ አቅርቦት፣ የብድርና የቁጠባ አገልግሎት እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤
- ወጣቶች በክፍለ ከተማው አስተዳደር የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጥምረት ይሰራል፤
- ወጣቱን በመልካም ስነ ምግባር ለማነጽና የሀገር ፍቅር ስሜቱን ለማጎልበት የሚያስችል አሰራር ይዘረጋል፣ተግባራዊ ያደርጋል፤
- ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ ያበረታታል፤
- ወጣቶችን በሚመለከት ከልማት ስትራቴጂ አኳያ ተቃኝቶ በወጣ ፕሮጀክት ላይ በከተማው ውስጥ ከሚሰሩ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ይመሰርታል ፣ አፈፃፀማቸውን ይከታተላል ፣ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ያቀርባል፤
- የአካል ጉዳትና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ወጣቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት በሁሉም የልማት ስራዎች እንዲሳተፉ፣ ከተለያዩ ጥቃቶች መከላከል፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞቻቸው ለማስከበር ከሌሎች አካላት ጋር በትብብር ይሰራል፤
- የወጣቶች የሱስ ማገገሚያ ማዕከላትን ያቋቁማል፤ይከታተላል፤ ይደግፋል፤
- ነዋሪው በስፖርት ለሁሉምና በባህላዊ ስፖርት ተሣታፊና ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤
- ለስፖርት ተግባራት የሚውሉ የስፖርት ትጥቆችና መሣሪያዎች አቅርቦት የሚሟላበትን ሁኔታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ያመቻቻል፤
- አግባብ ባለው ህግ የስፖርት ህክምና አገልግሎት መደራጀቱን፣ በስፖርት አበረታች መድሃኒቶችና ዕፆች መጠቀምን ለመከላከል የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን ይከታተላል፣ ያረጋግጣል፤
- የስፖርት ልማት ፈንድ የሚቋቋምበትን እና ባለሀብቱ በስፖርት ኢንቨስት የሚያደርግበትን ስልት ይቀይሳል ሲፈቀድም ተግባራዊ ያደርጋል
- የስፖርት ማህበራት ያደራጃል፤ የማዘውተሪያ ስፍራ አጠቃቀም የአሰራር ስርዓት ይዘረጋል፤ የስፖርት ማህበራትንና ክለቦችን እንዲሁም ጅምናዚየሞችን ይመዘግባል፤ የምዝገባ የምስክር ወረቀትና አስፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣል፤
- በሳይንሳዊ ጥናት ላይ የተመሰረቱ የስፖርት ማሰልጠኛ ዘዴዎችን በማዘጋጀት ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞች የስፖርት ዳኞችና የመሳሰሉት እንዲሰለጥኑ ያደርጋል፤
- የክፍለ ከተማውን ነዋሪ የስፖርት ተሳትፎ ለማጎልበት ያቅዳል፤ የስፖርት ውድድሮችንና የመዝናኛ ትርዒቶችን ያዘጋጃል፤ ይመራል፤ ከሚመለከተው ጋር በመተባበር የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር እንዲስፋፋና እንዲጠናከር ያደርጋል፤
- የአካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጎት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በስፖርት ያላቸው ተሳትፎ እንዲጎለብት አሰራር ይዘረጋል፤ ተግባራዊ ያደርጋል፤
- በውጭ ኦዲተር የተመረመረ የሂሳብ ሪፖርት ከማህበሩ እንዲቀርብለት በማድረግ የስፖርት ማህበራት ገቢ ለአላማቸው ብቻ መዋሉን ያረጋግጣል፤
- የአስተዳደሩን ስፖርትና መዝናኛ ምክር ቤት በየደረጃው በማቋቋም አግባብ ባለው ህግ አደረጃጀቱን ያጠናክራል፤ ይመራል፤ ይቆጣጠራል፡፡
- የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ከታችኛው የእድሜ እርከን የሚጀምርበት ስልት ይቀይሳል፤ ተግባራዊ ያደርጋል፤
- በክፍለ ከተማ ደረጃ የብዙሃን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የስፖርት መዝናኛ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ ያደርጋል፤ ያስተባብራል፤ ይመራል